• Call Us
  • +25146 554 16 87

የቢሮ ኃላፊ መልዕክት

                                                                              የተከበሩ አቶ ኡስማን ሱሩር

                                                      በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና                           

                                                                         የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መልዕክት

 

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ሴክተር ዋና ዓላማ በክልሉ የሚታየውን የግብርና ምርታማነት ማነቆዎችን በመፍታት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል ከፍተኛ የግብርና ምርት ግብ ማሳካት ሲሆን ዝርዝር ዓላማዎቹም የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የገቢ ምርት መተካት፣ የወጪ ምርትን በአይነት በብዛት ማሳደግ፤ ለግብርና ኢንደስትሪዎች በቂ ምርት ማምረት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋት እንደዚሁም በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ድህነትን ማሸነፍ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ያለፉት ጥቂት ዓመታት የተቀናጀ ግብርና ልማት ጉዟችን የተለጠጡ ግቦቻችንን ለማሳካት ባደረግነው ርብርብ ሰፊ አቅም የገነባንበት፣ በፈጠራ የታገዙ አዳዲስ ኢኒሺዬቲቮች ተቀርፀው በመተግበራቸው የተመዘገበ ውጤት በፈፃሚውና በህዝቡ ውስጥ የይቻላል መንፈስ የተፈጠረበት፣ በሁሉም ዘርፎች ሊሠፉ የሚችሉ ምርጥ ልምዶችም የተገኘበት፣ ዘርፉ ከነበረበት አነስተኛ የእድገት ደረጃ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ምርትና ምርታማነት እድገት የተመዘገበበት፣ የነበረው የድህነት ደረጃ የመቀነስና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናም በማሻሻል ረገድ የላቀ ውጤቶች የተመዘገበበት ዘመን ነበር። በቀጣይ አመታትም በመሪ እቅዳችን ዉስጥ የተቀመጡ ግቦቻችንን በማሳካት፣ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣትና የምግብና ስርዓተምግብ ዋስትናን ለማዘጋገጥ ተግተን እንሰራለን።

ይህ ድህረ ገጽ የተዘጋጀው የክልሉ የግብርና ልማትን በተመለከተ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች የግብርና ዘርፍ ተዋናዮች በቀላሉ መረጃ ማግኘት፣ ልምድ መለዋወጥ በሚያስችል መንገድ መረጃዎችን ለማጋራት ሲሆን በተለይም የክልላችንን የግብርና ዘርፍ በዘላቂነት ለማሳደግ የምንከተለው አላማ፣ ተልእኮ እና ራዕይ፣ የግብርና ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን፣ የተለያዩ የግብርና ዘርፎች የሚመለከቱ መረጃዎች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የምርምር ውጤቶችን እናካፍላለን። ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በወቅቱ እናጋራለን።