CERS-Bureau of Agriculture
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ሴክተር የ2017 የግማሽ አመት የዋና ዋና ግቦች አፈፃፀም ግምገማና ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ የሴክተሩ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩም ባለፉት 6 ወራት የተቀናጀ ግብርና ለቤተሰብ ብልጽግና ተብለው የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ውጤት እያመጡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ኡስማን ሱሩር በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት በክልሉ በቀጣይ ጊዜያት በግብርናው ዘርፍ በሁሉም መስክ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በየዘርፉ የሚታዩ የምርታማነት ልዩነቶችን ማጥበብ አርሶአደሮቻችን ተቀራራቢ የምርታማነት ደረጃ ላይ እንዲመጡ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
መላውን ህብረተሰብ በማንቀሳቀስና በተቀናጀ መንገድ በመምራት የተቀናጀ ግብርና ለቤተሰብ ብልጽግና ተብለው የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።
የተቋም ግንባታ ሥራ በትክክለኛ ሀዲድ ውስጥ ገብቷል ያሉት አቶ ኡስማን የምርታማነት እድገት መጨመሩ፣ በክልሉ የምርት ወቅቶች ከ3 ወደ 5 ማደጋቸውን በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በጸደይ ወቅት 22ሺህ ሄ/ር በሽምብራ መሸፈኑን በአብነት በመጥቀስ አስረድተዋል።
በየዘርፉ ተስፋ የሚሰጡ ተጨባጭ ውጤቶች ቢኖሩም እነዚህን ስኬቶች ማስፋት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ ያሉት ኃላፊው በሞዴል አርሶ አደር ደረጃ የተገኙ አመርቂ ውጤቶችን ቀምሮ ማስፋት የወቅቱ ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
ክልል አቀፍ ኢንሼቲቮችም ሆነ እንደ ሀገር በልዩ ሁኔታ በመተግበር ላይ ያሉ የልማት ስልቶች ውጤታማነት የዘርፉን ተስፋ በአግባቡ የሚያመላክቱ መሆናቸውን የገለጹት የቢሮ ሃላፊው እነዚህ ውጤቶች ወደ በሁሉም አካባቢና ግለሰብ እንዲሰፉና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል። የሚታዩ ክፍተቶችን እያረሙ ለተሻለ ውጤት መንቀሳቀስ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ የልማት ወቅቶችን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም፣ የጊዜ፣ የሀሳብና የተፈጥሮ ሀብት ምርታማነትን ማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የመሬት አጠቃቀም ስርኣትን ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ከዘርፉ እንደሚጠበቅም አቶ ኡስማን አብራርተዋል ።
በየጊዜው እየሰፋ የመጣውን የአፈር አሲዳማነት ችግር ለመቅረፍ የኖራ አቅርቦትን ማጠናከርና ችግሩን ሊቋቋሙ በሚችሉ የሰብል አይነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ተብራርቷል።
በቀጣዮቹ የምርት ዘመኑ ጊዜያት እንደ በልግ፣ መኸርና አረንጓዴ አሻራ ያሉ ወሳኝ ተግባራት እንዳሉ ያነሱት የቢሮ ሃላፊው ይህን የሚመጥን የተቀናጀ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
እንደ ዘርፍ የከተማ ግብርናን በልዩ ሁኔታ በመፈጸም በትንሽ መሬት ተጨማሪ የግብርና ምርት ለማምረት፣የአረንጓዴ አሻራን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ፣ የግብኣት በተለይም የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን ለማሳለጥ፣የግብርና እሴት ሰንሰለትን ለማሳደግ፣ የተቀናጀ ግብርናን በቤተሰብ ደረጃ ለመተግበርና የዘርፉን ስኬቶች በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለማጉላት በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል ።
በመጪው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልዩ የቡና ልማት መርሃ በመተግበር አንድ አርሶ አደር ቢያንስ 250 የቡና ችግኝ እንዲያለማ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
Copyrights 2025. . Centeral Ethiopia Bureau of Agriculture. All Rights Reserved.
Developed by CE-SCIENCE AND INFORMATION TECHNOLOGY BUREAU